ለባዊነት
ሰብዓዊነት ልዩ ጸጋ ነው፡፡ በፈጣሪ ዐምሳል ለተሰራው ለሰው ልጅ ብቻ የተሰጠ ታላቅ ገጸ በረከት፡፡ ሰብዓዊነት ሰው መሆን ነው፡፡ የተፈጥሮ አካል ሆኖ ተፈጥሮን በአጽንኦት የማሰተዋል ልዩ ጥበብ፡፡ ሰብዓዊነት ክብር ነው፡፡ የማመዛዘን ብቃት ለብቻው ለተሰጠው ሃያል ፍጡር የተቸረ የችግር ባህር መሻገርያ በትር፡፡ ሰብዓዊነት ካበረከታቸው ነገሮች መካከልም ትንሹ የቋንቋ ተጠቃሚ ብቸኛው ፍጡር ሰው እንዲሆን ማስቻሉ ሊሆን ይችላል፡፡ የቋንቋ ተመራማሪዎች ይህንን ሀያል ቃል ከቐንቐ ባህርያት መካከል ሰድረውታል፡፡ መመኪያ ሳይሆን እውነታ እንዲሆን በማሰብ፡፡ ሀሰት ሳይሆን ርቱዕ ክብር እንደሆነ በማመን፡፡
ሰብዓዊነት ውስጥ መልካምነት በኖርንበት አካባቢና ባሳደገን ማህበረሰብ ተቀርፆ ይቀመጣል፡፡ ሀገራዊ ማንነትም በዚህ ውስጥ ትልቅ ስፍራ አለው፡፡ ሁላቸንም ከቤተሰብ ና ከማህበረሰብ አልፎ በሀገራችን እሴቶች እንቀረጻለን፡፡ በምናደንቀው የጥበብ ስራ ውስጥ የሀገራችንን ስም ስንሰማ ደምስሮቻችን ውስጥ የሚሮጠውን ደማችንን ከማቆም አልፎ የሚያዘልለው እንደአንድ ሀገር ህዝብ የምንመገበው ምግብ ሳይሆን ሰብዓዊነት ያዘለው ኢትጵያዊ ማንነት ውስጥ የሚገኘው የመልካም እሴት ቅራጭ ነው፡፡ እንደአንድ በቅን ልቦች ተከቦ እንዳደገ ኢትጵያዊ መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ መቻቻልን፣ አብሮነትን፣ መተባበርንና ጥበብን መቃረማችን ግልጽ ነው፡፡ ያሳደገን ማህበረሰብ ክቡሩን የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ከኛ ይልቅ የህይወት ልምዶችን ያካበተውን ታላቃችንን ማክበርን አስተምሮናል፡፡ ያለመበላለጥ በእኩልነት ሚዛን እንድንቆም ሸንጎውን መስርተው አውርሰውናል፡፡
ሰው ሰው ከተሰኘ በኃላ የተሰጡትን ፀጋዎች የሚጠቀምበት ቀልፍ ማስተዋል ነው፤ ለባዊነት፡፡ ለባዊ የጥበብን ሚሰጢር ከስልጣኔ እያዋጀ የተጎነጨ አስተዋይ ነው፡፡ በመሆኑም ለባዊ የፍትህ ሸንጎን ተክሎ፣ ከልጅ ልጅ ቢለዩ አመትም አይቆይም በሚል የአካቶ ትምህርትን አማልቶ፣ አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል እያለ አብሮነትን ሰብኮ፣ ከአለም ሳንርቅ ኢትጵያዊነት እንዲሰርጽብን ኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሰረተ አለማቀፋዊነትን አስተምሮ የመፍትሄው አካል እንድንሆን የተጋ የሀገራችን መልካም እሴቶች ድንቅ ዳራ ነው፡፡
ሜሮን
ታህሳስ 18ቀን 2011 ዓ.ም